40 ሺህ ተሳታፊዎችን ያስተናገደው ይህ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ታዋቂ የውጭና የሀገር ውስጥ አትሌቶች ተገኝተዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ከሚከናወኑ የጎዳና ላይ ታላላቅ ውድድሮች መካከል ከአፍሪካ በአንደኝነት በዓለም አቀፍ ደግሞ በስድስተኝነት የሚጠቅስ ሲሆን ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የተለያዩ የውጭ ቱሪስቶች እና አትሌቶች በተወዳዳሪነት እየተሳተፉበትም ይገኛሉ። በዚህም ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ በክብር እንግድነት እንዲሁም ሁለት የዩጋንዳ አትሌቶች ደግሞ በተወዳዳሪነት ተሳትፈዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ እየሆነ የመጣ ሲሆን ዛሬ በተካሄደው ታላቁ ሩጫ ውድድር የውጭ ቱሪስቶች በታደሙበት በዚህ ዕለት የቱሪዝም ሚኒስቴር በቦታው ላይ በመገኘት ሀገራችን ኢትዮጵያ የታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ባለቤት እና የታዋቂ አትሌቶች መፍለቂያ ምድረቀደምት ሀገር መሆኗን ለተሳታፊ ቱሪስቶች የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል።