ቱሪዝም ሚኒስቴር ዘንድሮ የሚካሄደውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ውድድር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቂያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የቱሪዝም ሚኒስቴር ገልጿል።
እሁድ የሚካሄደው የ2015 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ተሰጥቷል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የገበያ ልማትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው አትሌቶች መፍለቂያ ናት ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የስፖርት ቱሪዝም አቅም ለመጠቀም የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን እያዘጋጀ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
አትሌት አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ካሸነፈበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ መድረኮች በምታስመዘግበው ስኬት የአፍሪካ ኩራት ሆና ቀጥላለች ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልጸዋል።
አትሌቲክስ ከውድድር ባለፈ መልከ ብዙ የሚባሉ ፋይዳዎች አሉት፤ በዚህ ረገድም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ በኩል ያለውን አበርክቶ ጨምረው ጠቅሠዋል። በውድድሩ የስፖርት ምርቶችን በመሸጥ የስፖርት ቱሪዝም ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባና ለዚህም ቱሪዝም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ታላቁ ሩጫ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሳተፍ ሀገሩን ለዓለም ማስተዋወቅ እንዲችል ክብርት ሰላማዊት ጥሪ አቅርበዋል ። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ ውድድሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፍሪካንና የተቀረውን ዓለም ቀልብ እየሳበ ይገኛል ብሏል። ውድድሩ በቱሪዝም፣ በኢኮኖሚ፣ ተተኪ አትሌቶች በማፍራትና በሌሎች መስኮች ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ እንደሚገኝና ይሄንን ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክቷል።
የፊታችን እሁድ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር 40 ሺህ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 500 አትሌቶች እንደሚወዳደሩ ታውቋል። ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተጨማሪ በወንዶች ኬንያውያኑ ቪክቶር ሙቲና ቪክቶር ኪፕሩቶ እንዲሁም ዩጋንዳውያኑ ኬኔት ኪፕሮፕና አላን ኪቤት ይወዳደራሉ። ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ በውድድሩ ላይ በክብር እንግድነት ይታደማሉ። በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊዎች 255 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል።
መረጃዎቻችንን በትዊተር፡ https://twitter.com/motethiopia
በቴሌግራም፡ https://t.me/tourismethiopia
አድራሻዎቻችን ያገኟቸዋል።