የሀረር ከተማ የአለም አቀፉ የሀር መንገድ የቱሪዝም ጥምረት አባል ከተማ ሆና ተመርጣለች።
ከተማዋ የዚህ አለም አቀፍ የቱሪዝም ጥምረት አባል መሆኗ በአለም የቱሪዝም መስክ የጎላ ትኩረት እንድትስብ፣ ጎብኚዎችን ከተለያየ የአለም ክፍል ለመሳብ እና የከተማዋን ታሪካዊ ቅርሶችና የቱሪዝም መስህቦችን በይበልጥ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር በትብብርና በጋራ ለመስራት፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ልምድ ለመለዋወጥና የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን በይበልጥ ለማልማት ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ሀረር ከተማ የዚህ ታሪካዊ ጥምረት አባል ልትሆን የቻለችው በቻይና ሉዣን ከተማ በተካሄደው የ2026 የሀር መንገድ የቱሪዝም ጥምረት አባል ከተሞች አመታዊ አለም አቀፍ የጉዞ ኤጀንቶች ኮንፈረንስ ላይ ነው።
ታሪካዊዋ የሀረር ከተማ በአለም አቀፉ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ አለም አቀፍ ቅርሶች ባለቤት ስትሆን፣ የአለም የቅርስ ከተሞች ድርጅት እና የአለም የቱሪዝም ከተሞች ፌደሬሽን አባል መሆኗም ይታወሳል።
