የጳጉሜ 2ን ቀን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል ሀገራዊ ፓናል ውይይት ተካሄድ።

በሀገሪቱ የኢኮኖሚ አዕማድና የዕድገት ምዕራፍን የሚያፋጥኑ አበይት የልማት ዘርፎችና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የፓናል ውይይት ተካሄደ።

በቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ ፓናል መድረክ ላይ በሀገሪቱ እየተመዘገቡ ያሉ የሪፎርም ውጤቶችንና የወደፊት የልማት አቅጣጫዎችን ተዳሰሷል።

በመድረኩ ላይ በስፋት ከተነሱት ነጥቦች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ ቀደም ሲል ከነበረበት የማህበራዊ ዘርፍ ፈርጅ ወጥቶ አሁን ላይ ሀገሪቱን ወደፊት ከሚያሸጋግሩ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አዕማድ አንዱ ሆኖ መዋቀሩ ትልቅ ዕድል መፍጠሩ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የመሠረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ሥራዎች መስፋፋት የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ማጋዘታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ለግሉ ዘርፍ አቅጣጫ የሚያሳዩ (Benchmark) በመሆናቸው የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ መንገድ የሚከፍቱ መሆናቸው ተብራርቷል።

ፓናሉ ላይ የሀገራዊ ማንሰራራት እና የሜጋ ፕሮጀክቶች ትግበራ ማሳያ ተደርጎ ከተጠቀሱት መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግዙፉ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስና በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን የአቪዬሽን የበላይነት የበለጠ የሚያጠናክር፣ የሀገሪቱን የማንሰራራት ጉዞ በተግባር የሚያሳይ እና ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት የሚጥል መሆኑ ተመልክቷል።

በፓናል ውይይቱ ላይ በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች የተሰማሩ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የታደሙ ሲሆን ፕሮፌሰር ወራሽ ጌታነህ (ከማዕድን)፣ ዶ/ር በቀለ ንጉሴ (ከከተማ ልማት)፣ ዶክተር ሚካኤል መሐሪ (ከውሃና ኢነርጂ)፣ ዶ/ር ፍትህ ወ/ሰንበት (ከቱሪዝም) እና ዶ/ር ተመስገን ዋለልኝ (ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ) በፓናሊስትነት ከተሳተፉት መካከል ይገኙበታል።