በሀገሪቱ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችና  የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ:-

ጳጉሜ 2 — “የማንሰራራት ቀን”ን በማስመልከት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ እና የተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የሚያስቃኝ የፎቶ አውደ-ርዕይ ለህዝብ እይታ ቀረበ።

አውደ-ርዕዩ በስድስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በስራቸው ስር ባሉ ተቋማት የተከናወኑ እና በሂደት ላይ የሚገኙ ታላላቅ የልማት ስራዎችን ያካተተ ሲሆን፣ የቀረቡት ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ፣ የመሠረተ ልማት መስፋፋት እና የህዝብ አገልግሎት መሻሻል ላይ እየፈጠሩ ያሉትን የመጡ ለውጦች የሚያሳዪ ናቸው።

በአውደ-ርዕዩ በተለይ በቱሪዝም ልማት፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በግብርና፣ በማአድን ቁፋሮ፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፎች የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ቀርበዋል።
በተጨማሪም የተጠናቀቁና አገልግሎት ላይ የዋሉ ፕሮጀክቶች ከሀገራዊ ልማት ግቦች አንፃር ያላቸውን አስተዋፅኦ በፎቶ እና በመረጃ ተደግፈው ቀርበዋል።

የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ የቀረቡት የልማት ስራዎች የተቋማትን የአፈጻጸም ውጤት ከማሳየት ባለፈ ለህዝብ ፍላጎቶችና ፍላጎት-ተኮር ልማት ምላሽ ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶችንም ያንጸባርቃሉ ተብለዋል።

በቅርብ ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እና በመንግስት፣ በህዝብ እና በግሉ ዘርፍ መካከል የተፈጠረውን የጋራ ትብብር ውጤት የሚያሳዩ መሆናቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ሀገራዊ ራዕዮችን ለማሳካት የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የህብረተሰቡ ተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።  

በመጨረሻም የተመዘገቡት ስኬቶች አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ፣ በተጠናከረ መነቃቃት እና በተሻለ የልማት አቅም ለመጀመር አበረታች መሠረት እንደሚሆኑ ተመልክቷል።