የኢትዮጵያ ማንሠራራት በቱሪዝም ዘርፍ..

ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ በባህላዊ ቅርሶቿ፣ በተፈጥሯዊ ሀብቶቿና በሕዝቦቿ ብዝሃነት በዓለም ላይ ልዩ ቦታ ያላት ሀገር ናት።

ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት ያህል ይህ እምቅ የቱሪዝም አቅም በሚገባ ሳይጠቀምበት ቆይቷል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ግን የቱሪዝም ዘርፉ ከቀድሞው የተለየ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል።


በፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ በመዳረሻ ልማት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በቅርስ ጥበቃና በዓለም አቀፍ ገጽታ ግንባታ የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻነት እያሸጋገሯት ይገኛሉ።


የለውጡ ጉዞ በተለይ በመዳረሻ ልማት መስክ በግልጽ ሁኔታ ታይቷል። በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በትውልድ ፕሮጀክቶች ስር የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቀደም ሲል የተዘነጉ ወይም ያልለሙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ዘመናዊና ማራኪ መዳረሻዎች ቀይረዋል። የወንጪ ሐይቅ፣ የሀላላ ኬላ፣ የጎርጎራ፣ የኮይሻና ሌሎች መዳረሻዎች የቱሪዝም ልማት ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ አድርጓል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ቱሪዝም የመዝናኛ ብቻ ሳይሆን የልማትና የሕዝብ ተጠቃሚነት መሣሪያ መሆኑን አሳይተዋል።



በተመሳሳይ ጊዜ የከተሞች ኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን የከተማ ገጽታ እየቀየረ ይገኛል። በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የተከናወኑ የመንገድ፣ የአረንጓዴ ቦታ፣ የእግረኛ መንገድና የመዝናኛ ስፍራዎች ልማቶች ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ሲያደርጉ ለውጭ ጎብኚዎችም የሚስቡ እያደረጓቸው ነው። ይህም የከተማ ቱሪዝምን በአዲስ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።
የቱሪዝም ማንሠራራቱ በመሠረተ ልማት መስክም ትልቅ እመርታ አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአቪዬሽን መሪ ተቋም በመሆን አዳዲስ የበረራ መስመሮችን በመክፈትና የአየር ማረፊያዎችን በማዘመን የቱሪዝም ፍሰትን አሳድጓል። ከዚህ ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ የሆቴል ብራንዶች መግባታቸውና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ ያደረጉት ኢንቨስትመንት የእንግዳ ተቀባይነት አቅምን በእጅጉ አሳድጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆኑ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ቱሪስቶችን በተሻለ አገልግሎት የማስተናገድ አቅም አላት።

የታሪክና የባህል ቅርሶች ጥበቃ እና እድሳትም የለውጡ ዋና ምሰሶ ሆኗል። የጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግሥት፣ የጎንደር ፋሲለደስ አብያተ-መንግሥታት፣ የሐረር ጥንታዊ ቅርሶችና ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎች በጥንቃቄ እንዲጠበቁ ተደርጓል። ይህ ሥራ ቅርሶቹን ለትውልድ ከማስተላለፉ ባሻገር የቱሪዝም ሀብት እንዲሆኑ አስችሏል። በተጨማሪም የማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም በመስፋፋቱ አካባቢያዊ ማኅበረሰቦች ከቱሪዝም በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ያላትን እድል በመጠቀም በMICE Tourism ዘርፍ ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች። ዘመናዊ የኮንፈረንስ ማዕከላት፣ የኤግዚቢሽን አዳራሾችና የስብሰባ ተቋማት መገንባታቸው የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ አቅሟን አሳድጓል።


ይህም ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት ዘርፍ፣ ለንግድ ተቋማትና ለአገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፈጥሯል።


እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የሚያሳዩት ቱሪዝም የመዝናኛ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገት፣ የሥራ ፈጠራ፣ የገጽታ ግንባታና የባህል ዲፕሎማሲ ሀይል መሆኑን ነው። በቱሪዝም የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ኢኮኖሚውን ሲደግፍ፣ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ደግሞ ለሺህዎች ዜጎች የኑሮ መሠረት ሆነዋል።


በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን አወንታዊ ገጽታ ለማጠናከር ቱሪዝምን እንደ ለስላሳ ኃይል (Soft Power) በተሳካ ሁኔታ እየተጠቀመችበት ነው።

የUN Tourism ዕውቅና ያገኙ የኢትዮጵያ መንደሮች፣ በዓለም አቀፍ የጉዞ መድረኮች ላይ የሚገኘው ተሳትፎ፣ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ኢትዮጵያ በቱሪዝም ካርታ ላይ ያላትን ቦታ እያጠናከሩት ይገኛሉ። ይህም ሀገሪቱ የቱሪዝም ልማትን ከተፈጥሯዊ ሀብት ጥበቃ፣ ከማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና ከዘላቂ ልማት ጋር በማስተሳሰር የተሳካ ሞዴል ለመገንባት እየሰራች መሆኗን ያረጋግጣል።


በመደምደሚያ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ማንሠራራት የአንድ ዘርፍ ስኬት ብቻ ሳይሆን የሀገር ግንባታ ታሪክ ነው። የመዳረሻ ልማቶች፣ የኮሪደር ልማቶች፣ የቅርስ ጥበቃ ስራዎች፣ የአየር ትራንስፖርት እድገትና የእንግዳ ተቀባይነት አቅም ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻነት እያስጠጉአት ይገኛሉ። ይህ ጉዞ በተመሳሳይ ፍጥነት ከቀጠለ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ላይ ተፎካካሪ እና ተመራጭ መዳረሻ መሆኗ አይቀሬ ነው።