ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ወደር የማይገኝለት ውብ ተፈጥሮ፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እና አስደናቂ የመልክዓ-ምድር ጸጋ የታደለች ምድር ናት።
ሆኖም ይህ ግዙፍ እምቅ አቅም ለዘመናት በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል።
ዛሬ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥልቅ እይታና አመራር፣ ሀገራችን የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ወደ ማይነጥፍ የኢኮኖሚ ምንጭነት በመቀየር ላይ ናት።

ኢትዮጵያ በተለይ በኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍ አስደናቂ የሆነ ሀገራዊ ንቅናቄን እና ተጨባጭ ለውጥን እያስመዘገበች ትገኛለች።
ኢኮ-ቱሪዝም ከተለምዷዊው የጅምላ ጉብኝት ባሻገር፣ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሠረተ የቱሪዝም ንዑስ ዘርፍ ነው።
ይህ ዘርፍ ጎብኚዎችን ወደ ጥልቅ የተፈጥሮ ተመስጦ የሚመልስ እና ማኅበረሰብን በተፈጥሮ ጥበቃ ውስጥ እኩል አጋር አድርጎ ባህላዊ እሴቱን በኩራት እንዲጠብቅ የሚያስችል ትልቅ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው።
ከ17 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሀገራችንን የቆዳ ስፋት የሸፈኑት ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ቀጣናዎች፣ እንዲሁም በዩኔስኮ የተመዘገቡት በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን ኢትዮጵያን ለኢኮ-ቱሪዝም ልማት እጅግ ተመራጭ ያደርጓታል።
ይህን የተፈጥሮ ካፒታል ወደ ተጨባጭ ጥቅም ለመለወጥ ባለፉት 5 ዓመታት በመንግሥት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሀገራችንን የቱሪዝም ገፅታ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት ይገኛሉ።
ይህ ተጨባጭ ሀገራዊ ለውጥ የተጀመረው አዲስ አበባን ወደ አረንጓዴ እና ማራኪ መዲናነት በለወጠው የ”ገበታ ለሸገር” ሜጋ ፕሮጀክት ስኬት ነው።
አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ እና ሸገር ፓርክ የዚህ ራዕይ ቀዳሚ ማሳያዎች ሆነው አገልግለዋል።
ይህን አስደናቂ ስኬት ወደ ክልሎች ለማስፋፋት የተነደፈው የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ደግሞ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማሰባሰብ ወንጪን፣ ጎርጎራን እና ኮይሻን በተሳካ ሁኔታ ወደ ታላላቅ የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻነት ቀይሯቸዋል።

በተለይም ወንጪ በዘላቂ የተፈጥሮ ጥበቃ እና በማኅበረሰብ አቀፍ ልማት ባስመዘገበችው ስኬት እ.አ.አ. በ2021 በዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) “ምርጥ የቱሪዝም መንደር” ተብላ መመረጧ የጥረቱ ተጨባጭ ፍሬ እና የዓለም አቀፍ ዕውቅና ማሳያ ነው።
የስኬታማው የልማት ቅብብሎሽ አዲስ ምዕራፍ የሆነው የ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት በሀገራችን 8 ልዩ ቦታዎች ላይ ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጡ ኢኮ-ሎጆችን በማስገንባት ላይ ይገኛል።
የፕሮጀክቱ ዋና መነሻ በጀት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ የሽያጭ ገቢ ነው።
በሂደቱም የግል ባለሀብቶች በዘርፉ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በር ተከፍቷል። የዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ውጤት ሆኖ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተመረቀው ደንቢ ኢኮ ሎጅ ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ የተገነባው ደንቢ ኢኮ ሎጅ፣ የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ የከተማ ፍልሰትን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይገኛል።
የአፋርን ልዩ የመልክዓ-ምድር ውበት አጉልቶ የሚያሳየው ኒን ሊ ፓልም ሎጅ ሌላኛው የገበታ ለትውልድ ትሩፋት ነው።
ኒን ሊ ፓልም ሎጅ “ሰማያዊ ዓይን” የተሰኘውን ተፈጥሯዊ የፍል ውኃ ገንዳ እና ሰው ሠራሽ ሐይቆችን በማካተት የተፈጥሮን እና የዘመናዊነትን ውህደት አሳይቶናል።
በሶማሌ ክልል በ385 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ሸበሌ ሪዞርት፣ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ጠብቆ እና ባሕላዊ የግንባታ ጥበብን በማሳተፍ የተሠራ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ፈርጥ ነው።
በሐይቅ እስጢፋኖስ ዳርቻ ያረፈው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፣ የሀገራችንን ድንቅ ጸጋ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሌላኛው ዕንቁ መዳረሻ ነው።
በአርባ ምንጭ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጂማ በመገንባት ላይ ያሉት የኢኮ ቱሪዝም ማዕከላትም የዚሁ ስትራቴጂያዊ ልማት አካል ናቸው።
እነዚህ መጠነ-ሰፊ ጥረቶች እና ተከታታይ ግንባታዎች ኢትዮጵያ በዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዕውቅና እንድታገኝ አስችለዋታል።
መንግሥት እነዚህን የልማት ትሩፋት በፖሊሲ ደረጃ በዘላቂነት ለመደገፍ ቀደም ሲል የነበሩ ስትራቴጂያዊ የአፈፃፀም ክፍተቶችን በመቅረፍ አዲስ የቱሪዝም ፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ አድርጓል። ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ መዳረሻ የማድረግ ጽኑ ፍላጎትን ያሳያል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት “በመደመር” ፍልስፍና የሀሳብ ልዕልና እና በተግባር-ተኮር አመራር የኢኮ-ቱሪዝም እምቅ ሀብቷን ወደ ተጨባጭ ብልጽግና በመቀየር ላይ ትገኛለች።
ቱሪዝምን ከሥነ-ምህዳር ጥበቃ ጋር በማጣመር የተገነቡት እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ሀገራችን የተፈጥሮ ፀጋዋን ጠብቃ ማኅበረሰቧን ተጠቃሚ የሚያደርግ አረንጓዴ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ መሠረት እንድትገነባ አስችለዋታል።
የወደፊቷ ኢትዮጵያ የዓለምን ትኩረት የምትስብ እና ለትውልድ የሚሻገር የተፈጥሮ ሀብት ያላት የኢኮ-ቱሪዝም የምድር ገነት ሆና መውጣቷ አይቀሬ ነው!
ከኢቢሲ ዘገባ የተወሰደ