የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት አመራርና ስራተኞች ጋር በመሆን “ትዉልድን በስነ-ምግባር ፤ ተቋምን በአስራር” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለውን 22ኛው የጸረ-ሙስና ቀን በዘርፍ ደረጃ አከበረ::

በመድረኩ በመገኝት የመክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ድኤታ እንደገና አበበ (ዶ.ር) እንደተናገሩት ቱሪዝም ከአምስቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሠሦዎች አንዱ መሆኑን አንስተው፣ ቱሪዝም የራሱን የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማስቻል ፣ ላለፉት ዓመታት ውጤታማና ስኬታማ የተቋም ግንባታና ምቹ ከባቢ የሥራ ሁኔታዎች በመፍጠር፣ እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስፋት፣ በነባር መዳረሻ ላይ እሴት በመጨመር ፣ የዱር ሕይወት በመንከባከብ ፖሊስና ስትራቴጂ በመንደፍ፣ የቅርስ ጥበቃና ጥገና በማከናወን የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሲሰራ የቆየ መሆኑን ገልጸው ።
ነገር ግን ይህንን ስኬትና ውጤታማ ጉዞ ለማስቀጠል ከሙስና የጸዳ ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ ተቋማት ማደራጀትና መፍጠር ያሰፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
አክለውም በኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝም ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ኢንዱስትሪ እንዲሆን ለማስቻል ሙስናን የሚጸየፍ ሠራተኛ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና አገር መፍጠር ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል ።
በመድረኩ የከፍተኛ አመራሮች የሃብት ማሳወቅና ማስመዝገቢያ የሰነድ ርክክብ ሥነሥርዓት የተካሄደ ሲሆን ሚኒስትሮችና የተጠሪ ተቋማት ዳይሬክተሮች ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ተውካይ አስረክበዋል።

በመጨረሻም በሀገር አቀፍ ደረጃ በቀረበው የድምጽ ሰነድ ወይይት ተደረጎ ፣ ለቀረቡት ጥያቄና አስተያየቶች በረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ በአቶ ኪዳኔ ምህረት የጸረ ሙስና ኮሚሽን ተወካይ እና በአቶ ንጉሴ ክብሩ የሚኒስቴር ጽ/ቤት ኃላፊ መላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ።
