በሲዳማ ክልል ለሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሙያዎች እና የክልል የባህል እና ቱሪዝም መዋቅር ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ ደምሴ

 
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋማ ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል ለሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ መስጠት ጀመረ።
 
 
የስልጠናውን ማስጀመሪያ መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የቱሪዝም ዘርፍ ሀላፊ አቶ አበበ ማሪሞ እንደገለፁት ስልጠናው በሲዳማ ክልል የሚገኙትን የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችና የባህልና ቱሪዝም መዋቅር ሰራተኞች አቅም በመገንባት፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እና የባለሙያዎችን ሙያዊ ብቃት በማጎልበት የክልሉን ቱሪዝም ተወዳዳሪነት ለመጨመር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልፀዋል።
 
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ ደምሴ በበኩላቸው ሚንስቴር መ/ቤቱ ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ስልጠናውን መስጠት ሲያቅድ በዋናነት በክልሉ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ የተቀላጠፈና የተሳለጠ እንዲሆን በማድረግ ክልሉን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ዘላቂና ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪዝም ልማት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
 
 
የስልጠናውን ዋና ትኩረት ዓላማዎች አስመልክቶ ገለፃ ያደረጉት በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዴስክ ሀላፊ ወ/ሪት ዘርአየሁ እንዳለው እንደገለፁት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እና ምርጥ ተመክሮዎችን ለባለሙያዎቹ ማስተዋወቅ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ክህሎቶችን ማዳበር፣ እንዲሁም የደንበኞችን እርካታ ማረጋገጥ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የተዘጋጀ የማነቃቂያ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ስልጠናው በክልሉ ለሚገኙ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ስራ አስኪያጆች፣ ባለሙያዎች፣ በመንግስት መዋቀር ለሚገኙ ባለሙያዎች፣ በእንግዳ አቀባበል፣ በመስተንግዶ፣ በቤት አያያዝ እና በምግብ ዝግጅት፣ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ፣ የቱሪዝም ክበባት አመሰራረት፣የብቃት ማረጋገጥ ፣በደረጃ ምደባ ፣ በማይስ ቱሪዝም ፅንሰ ሀሳብ እንዲሁም የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሱፐርቪዥን ላይ ትኩረት በማድረግ ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ በተግባር ታግዞ እንደሚሰጥ ተገልጿል።