የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦፓርክ ጽንሰ ሀሳብ በኢትዮጵያና በቀጠናው ለማስተዋወቅ ያለመ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው።
ጂኦፓርክ እና ጂኦ ቱሪዝምን በኢትዮጵያ እና የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለውን ግንዛቤ እና ትግበራ ለማጠናከር ያለመ ጉልህ አህጉራዊ ወርክሾፕ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
 
በወርክሾፕ የመክፈቻ ንግግር ያቀረቡት የቱሪዝም ሚኒሰትር ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት በአለም ላይ 50 ሀገራት 229 የጅኦፓርክ በዩኔስኮ ቢያስመዘግቡም ከአፍሪካ ግን ሁለት ሃገራት ብቻ መሆናቸውን አንስተው፣ ይህ የሆነበት ምክንያት አፍሪካ ውሰጥ የጅኦ ቱሪዝም እና ጂኦ ፓርክ ሃብት ባለመኖሩ ሳይሆን በዘርፉ ያለው የግንዛቤ እጥረት፣ ቅንጅት እና የአቅም ግንባታ ስራዎች አለመስራቱ መሆኑን ገልጸዋል ።
 
አክለውም ኢትዮጽያ አፍሪካ ውስጥ በዪኔስኮ ብዝሃ ሃብት ካስመዘገቡት ሁለት ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቁመው ኢትዮጵያ 12 የሚዳሰሱ፣ 6 የማይዳሰሱና 5 ጥብቅ ባዪሰፌር በዩኔስኮ እውቅና ተሰጥቷቸው የተመዘገቡ ብዝሃ ሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
 
አንዲሁም መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱና አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ እንዲሆን መደረጉ የጂኦ ቱሪዝምን ለማጥናት፣ ለማልማት እና ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም በቅርቡ የሚጸድቀው ረቂቅ የቱሪዝም ፖሊስ የጂኦቲሪዝም ሀብቶቸን ለመጠበቅ፣ የጂኦ ፓርኮችን ለመመሰረትና ግንዛቤ በመፈጠር ስራዎቸን ለማሳለጥ ትልቅ አቅም አንደሚሆን ገልጸዋል።
 
ወርክሾፕን ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ ፕሮጀክቶችን ልማት በመደገፍ የጂኦሎጂካል ቅርሶችን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ የጂኦሎጂካል ቅርሶችን እንዲጠብቁ እና እንዲንከባከቡ ለማበረታታት ማቀዱን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶናውት ተናግረዋል።
 
ኢትዮጵያዊ በጂኦቱሪዝም በርካታ ሃብቶች ያላት ሲሆን ሶፈኡመር፣ ገርአልታ፣ ኮንሶ፣ አፋር ፣ ባሌ ተራሮችና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርኮች ተጠቃሽ ናቸው ።
 
በአውደ ጥናቱ የተለያዩ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ለሁለት ቀን የሚቆይ ይሆናል።