የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ እና በኢትዮጵያ ለ39ኛ ጊዜ መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ “የዲጂታል አጀንዳ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የቱሪዝም አዲስ ቅኝት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ክብርት ሰላማዊት እንገለጹት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በቱሪዝም ዘርፍ የጎብኚዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መረጃ ለመስጠት፣ የጉዞ ዕቅድና ቆይታ ለማቀላጠፍ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በተቀናጀ መንገድ ለማስተዋወቅ እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡
የአለም አቀፍ ቱሪዝም ቀን በማስመልከት አዲስ የቱሪስት መረጃ መስጫ ማዕከል ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በአሉን ከመስከረም 14 ጀምሮ እስከ 17 በተለያዩ ፕሮግራም የሚከበር ሲሆን ጎብኚዎችን ከአዲስ አበባ ወደ ቤኑና መንደር በባቡር ትራንስፖርት ተጠቅመው በመጓዝ የአንድ ቀን ቆይታ የሚያደርጉበት አዲስ የቱሪዝም ፕሮግራም መጀመራቻም ተገልጻል፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት በጎንደር ቤተ መንግስት እና በጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት የተከናወኑ የእድሳት ስራዎች ተጠናቀው “ሕይወት በቤተ መንግስት” በተሰኘ ፕሮጀክት ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረጉ ተነግሯል።
የአለም ቱሪዝም ቀን በጎንደር ከተማ ሲከበር ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነውን የመስቀል በዓል በጋራ ማከበርን ያካትታል።
የዘንድሮው የዓለም የቱሪዝም ቀን አከባበር የዲጂታል ቴክኖሎጂና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም ዘርፍ የሚያመጡትን አዳዲስ እድሎች በማሳየት ኢትዮጵያን እንደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ ለማስቀመጥ የሚያግዝ ሲሆን፣ በዘርፉ የሚደረጉ የዲጂታል ለውጦችን ለማበረታታት እና የጎብኚዎችን ተሞክሮ ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።