የኢትዮ-ሳውዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተሳታፊ ልዑካን ቤይኑና ኢኮ ሎጅን ጎበኙ!
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ-ሳውዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተሳታፊዎች፣ በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ዕድሎችን በቅርበት ለመመልከት እንዲችሉ የቤይኑና ኢኮ ሎጅን ጎበኙ።
 
 
 
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) እንደገለፁት የቱሪዝም ሚኒስቴር በያዘው አዲስ ስትራቴጂ መሰረት የመካከለኛው ምስራቅና ባህረ ሰላጤው ሀገራት የቱሪዝም እድሎችን በሚገባ ለመጠቀም እየሰራ እንደሆነ ገልፀው ለኢትዮ-ሳዑዲ መርሀ-ግብር ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ስላለው የቱሪዝም ሀብቶች እና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ማሳየት እና በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
 
በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉብኝቱ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የኢትዮ ሳውዲ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተከትሎ ተሳታፊዎች በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የቱሪዝም ልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ እና በዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማሳየት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
 
​በኢትዮ ሳውዲ የጋራ የንግድ ምክር ቤት ኃላፊ አቡዱ አል አጅሚ በበኩላቸው ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በማዕድን ዘርፎች ካላት ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም በተጨማሪ፣ በቱሪዝም ዘርፍም ያላትን እምቅ ሀብት መመልከታቸው እና በቀጣይ በሚኖሩ ግንኙነቶች ትብብሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚችል ጉብኝት እንደነበር ገልፀዋል።
​የልዑካን ቡድኑ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቤይኑና ኢኮ ሎጅን መጎብኘት፡ ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመመልከት በተለይ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት በመስጠትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ የተገነቡትን የቱሪዝም መዳረሻዎች መመልከታቸውና በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ ለሁለቱም አገሮች ኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚፈልጉ ጠቅሰዋል።
 
የኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማህበር ፀሀፊ አቶ መሀሪ መሰለ
በበኩላቸው አሁን ላይ በሀገራችን በስፋት እየተሰራበት የሚገኘው የኮንፍረንስ ቱሪዝም አዲስ እድሎችን ይዞ የመጣ በመሆኑ እንደ ማህበር በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
 
የጉብኝት መርሀ-ግብሩን የቱሪዝም ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።