ከሳውዲ አረቢያ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ ያለመ የትውውቅ ጉዞ (Familiarization Trip) በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በሪያድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ሚያዝያ 11 እስከ 15 ሲካሄድ የቀየው የሳዑዲ ዓረቢያ የቱሪዝም ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ቆይታ በስኬት ተጠናቋል።
የጉብኝቱ ዓላማ የኢትዮጵያን አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ለሳዑዲ ዓረቢያና ለባህረ-ሰላጤው ሀገራት እንዲሁም ለአለም ህዝብ በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ቁጥር ማሳደግ እና በዘርፉ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ነው።

ልዑካኑ በቆይታቸው በአዲስ አበባና አካባቢው የእንጦጦ ፓርክ እና የሽሮ ሜዳ ባህላዊ አልባሳት ገበያ የጎበኘ ሲሆን የቢዝነስ ትውውቅ (B2B) መድረክ አካሂደዋል።
በቢሾፍቱ እንደ ኩርፍቱ ያሉ ዘመናዊ ሪዞርቶችና ተፈጥሯዊ ውበቶችን መመልከት ችሏል።
በሐረር የጀጎል ግንብ፣ ጥንታዊ መስጊዶች እና አስደናቂው የጅብ ማብላት ትርኢት ጎብኝተዋል ።
በድሬዳዋ ታሪካዊው የባቡር ጣቢያ የሐሙዲ መስጊድ እና የድሬዳዋ ቤተ-መንግስት መጎብኘት ችሏል ።
በጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት የጉዞ ወኪሎች መካከል የቀጥታ ግንኙነት ተፈጥሯል፤ ይህም የቱሪስት ፍሰቱንና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል።
በተጨማሪም ልዑኩ የሀገሪቱን እውነተኛ ገጽታ፣ ሰላምና እንግዳ ተቀባይነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስተዋውቁ ዕድል ተፈጥሯል።
በጉብኝቱ ወቅት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የቤተሰባዊነት መንፈስ ተፈጥሯል።
ልዑካኑ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የተደረገላቸውን “ለጋስ አቀባበል” በማድነቅ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ “እንደ ቤተሰብ” መቆራኘታቸውን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ሰላም ያላቸውን መልካም ምኞት በመግለጽ፣ ላሳዩአቸው እውነተኛ ፍቅርና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበው ወደ ሀገራቸው በሰላም ተመልሰዋል።