የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ላይዘን ቢሮ በመተባበር ያዘጋጁት ከፍተኛ የዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በምስራቅ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፈርጥ በሆነችው ሀረር ከተማ ጉብኝት አድርገዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከአምባሳደሮችና አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር በመሆን በክልሉ የሚገኙ ሙዚየሞችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ መርሀ ግብሩ ከ40 በላይ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች እና አለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሚኒስተሯት፤ በተደረገው ጉብኝት በክልሉ የሚገኙ አስደማሚ የመስህብ ስፍራዎችን በተለይ ደግሞ ለሐረር የተሰጣትን አስደናቂ ቅርሶችን ተመልክተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከተመለከቷቸውም መካከል በተለይ ለዘመናት ተጠብቀው የቆየና በሙዚየሞች የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ ሃይማኖታዊና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ጽሁፎችና መጽሃፍት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግስት ሙዚየሞችን ጠብቆ በማልማትና በመንከባከብ ረገድ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሙዚየሞች አያያዛቸውና አቀራረባቸው አርአያነት ያለውና ልምድ የሚወሰድበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሐረር ሕያው ሙዚየም እንድትባል ካስቻላት መካከል ባሕላዊ ቤቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እያንዳንዱ ቁሳቁሶች ትርጉምና መልዕክት ያላቸውና አስደናቂ መሆናቸውን እንደተመለከቱም ጠቁመዋል።
ይህም ታሪካቸው ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲቆይ የሚያስችል መሆኑን ተናግረው፤ ሌሎችም በክልሉ የሚገኙ ሙዚየሞችን እንዲጎበኙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱና በጉብኝቱ ላይ የተካፈሉ አካላትን በመያዝ በተለይ ሙዚየሞችን ማበልጸግ ላይ የድጋፍ ስራ ይከናወናል ብለዋል።
