“ከአንኮበር እስከ ሐረር በር”፦ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ6 ከተሞች ውድድር በደብረ ብርሃን በድምቀት ተጀመረ::
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና “ከአንኮበር እስከ ሐረር በር” በሚል መሪ ቃል ሀገርን በሩጫ ለማስተዋወቅ የታቀደው የ6 ከተሞች የሩጫ ውድድር ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ በታላቅ ድምቀት ተካሂዷል።
 
በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ታላቁ ሩጫ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን እና ከልዩ ልዩ ስፍራዎች የመጡ የሩጫ አፍቃሪዎችን ተሳትፈዋል።
 
​የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ውድድር የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች በሩጫ አማካኝነት ለዓለም ለማስተዋወቅ እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ያለመ መርሃ ግብር እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል::
 
“ከአንኮበር እስከ ሐረር በር” የሚለው መሪ ቃልም የሀገሪቱን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስመሮች እርስ በእርስ የሚያስተሳስር በመሆኑ፣ ዛሬ በደብረ ብርሃን የተጀመረው መርሃ-ግብር ለቀሪዎቹ ከተሞች ትልቅ የመክፈቻ ምዕራፍ ሆኖ አልፏል።
 
በብርዳማዋ የደብረ ብርሃን ማለዳ የተሳተፉ ሯጮች በታላቅ ወኔ እና ደስታ ውድድሩን ያከናወኑ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለእንግዶቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። ይህ አይነቱ ስፖርታዊ መድረክ በደብረ ብርሃን መካሄዱ ለከተማዋ የንግድ፣ የባህል እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ አዲስ መነቃቃትን ከመፍጠሩም በላይ የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
 
የ2018 ዓ.ም. ‘ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ‘ በቀጣይ ሐዋሳ ፣ ጅማ ፣ በቆጂ ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረር ከተሞች ይካሄዳሉ።