ኢትዮጵያ የባህሎችና የመልክዓ ምድሮች ባለሕብረቀለም ውህድ ነች። ሰላማዊት ካሳ፦ የቱሪዝም ሚንስትር

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን 2ኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቅርስ ምርምር ጉባኤ ”ምርምር ለቅርስ ጥበቃና ልማት” በሚል ከድንቅነሽ ግኝት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ጋር በድምቀት ማካሄድ ጀምሯል።

የመርሃ ግብሩን ማስጀመሪያ መልዕክት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንደገለፁት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በመላ አገሪቱ ችላ ተብለው የቆዩ የባህል ቅርሶችን በመጠበቅና በመጠገን ረገድ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።
ኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ የተፈጥሮና የባህል ቅርስ ባለቤት የሆነች ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ በእውነትም የባህሎችና የመልክዓ ምድሮች ሞዛይክ ነች ብለዋል።

ዘርፉ ለረዥም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባውን ትኩረት አለማግኘቱን ጠቅሰው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስት ቅርሶችን ለመጠበቅና ለማልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

ቀደም ሲል ችላ ተብለው የቆዩ ቦታዎች አሁን ተጠብቀው ለህዝብ ክፍት መሆናቸውን በመግለጽ፤ አንድነት ፓርክና ብሔራዊ ቤተመንግስት ሙዚየምን ጨምሮ ሰፋ ያለ የባህል ቅርስ ልማት መሰራቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ወራትና ዓመታት በርካታ የቅርስ ቦታዎች ይከፈታሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ቅርስ ጥበቃ ያለ ጥብቅ ሳይንሳዊ ምርምር ውጤታማ አይሆንም ብለዋል።
 

ለሁለት ቀናት ቀጥሎ በሚውለው ጉባኤ ላይ 26 የሚሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎችና ምክረ-ሃሳቦች ይቀርቡበታል። ከተለያዩ የአለም አገራትና ተቋማት የተውጣጡ ከ300 በላይ ታዳሚዎች በአካልና በበይነ መረብ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡