
በ11ኛው የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ካውንስል (UNESCO Global Geoparks Council) መደበኛ ስብሰባ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጂኦፓርክ (Central Ethiopia Rift Valley Geopark) የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክነት እውቅና እንዲያገኝ በይፋ ጸድቋል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት ኢትዮጵያ ከሞሮኮ፣ ታንዛኒያና ቱኒዚያ በመቀጠል የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ እውቅና ያገኘች አራተኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።
ሀገራችን ይህንኑ ታሪካዊ ስኬት የሚያረጋግጠውን ይፋዊ የእውቅና ሰርተፍኬት በአውሮፓውያኑ ኤፕሪል 27 በይፋ እንደምትረከብ ይጠበቃል።
ይህ ዕውቅና ኢትዮጵያ በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶቿ፣ በጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶቿና በመካነ ብዝኃ ሕይወት(Biosphere Reserves)ሀብቷ ከምትታወቅበት የተፈጥሮ፣የታሪክና የባህል ቅርስ ሀብት ባሻገር፣ በጂኦፓርክና በጂኦ-ቱሪዝም ዘርፍም አዲስ ምዕራፍ እንድትከፍት ዕድል ይፈጥራል።
እስካሁን በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀመችበትን የጂኦሎጂካል ቅርስ ሀብቷን ለቱሪዝም ልማት፣ ለሳይንሳዊ ጥናትና ለዘላቂ ልማት በማዋል ከፍተኛ እመርታ እንድታስመዘግብ ያግዛል።