የቀደሙ አባቶቻችን ክብር የትውልድ ኩራት ነው፡፡ የዛሬው ትጋት ደግሞ የነገው መተኪያ የሌለው ቅርስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማዕዘን፣ የሰው ዘር በኩር መገኛና የታሪክ ማኅደር መሆኗን ዓለም አውቆት፣ እኛም ደግመን ደጋግመን ተርከነው የኖርነው እውነት ነው።
ሆኖም ግን “ያለፈው ታሪክ ለዛሬ ስንቅ እንጂ መኖሪያ አይሆንም” እንደሚባለው በትናንት ታሪክ ማማ ላይ ብቻ ተቀምጦ መኖር የጉዞ መዳረሻን አያሰፋም።

ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ የታሪኳን አቧራ አራግፋ፣ የተፈጥሮ ዝናዋን በሥራ ጥበብና በፈጠራ አድሳ የቱሪዝም ተስፋዋ እንደ አዲስ ፋክቶ የሚታይበት የትንሳኤ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ትናንት በሙዚየሞችና በጥንታውያን ገዳማት ብቻ ዓይኑን ጥሎብን የነበረው ዓለም ዛሬ በጉልበትና በእውቀት በለሙት አዳዲስ መዳረሻዎቻችን ሳቢያ ቀልቡን ወደ እኛ መልሷል።
ይህ የቱሪዝም ሽግግር ለሀገራችን የኢኮኖሚ ሞተር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነትን አዲስ ከፍታ ለዓለም የምናሳይበት የገጽታ ግንባታችን አውራ መንገድ ሆኗል። “ጉልበት ካለ ድንጋይም ይፈጫል፤ እውቀት ካለ ምድርም ይለማል” ነውና የኢትዮጵያ የቱሪዝም ጉዞ ከነበረበት የቆመና ታሪክን ብቻ ከመተረክ ወጥቶ ወደ ተንቀሳቃሽ ልማት ተሸጋግሯል። በዚሁ እውነት መሠረት፣ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን ከኮንክሪት ጫካነትና ከትካዜ ድባብ አውጥተው ወደ አረንጓዴ፣ ሕያውና ሳቢ የቱሪስት ማዕከልነት ቀይሯታል።
ይህ ስኬት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይወሰን ወደ ክልሎች ተሻጋግሮ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በዕውቀትና በሥነ-ሕንጻ ጥበብ በመደመር እሳቤ በማልማት ለዓለም ዕይታ ማብቃት ተችሏል። እነዚህ ልማቶች መሬት ላይ ያለውን እምቅ ሀብት ከዘመኑ የፈጠራ ጥበብ ጋር በማቀናጀት የነገውን ትውልድ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የብልጽግና ተምሳሌቶች ናቸው።
ከዚህም ባሻገር አሁን ላይ በአዲስ ጉልበት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞቻችንን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዋነኛ ማነቆ የነበረውን የመሰረተ ልማት ምቾት እጥረት በዘላቂነት የፈታ ታላቅ ሀገራዊ ሥራ ነው።

“መንገድ ካለ አገር አለ” እንዲሉ ጽዱና ሰፋፊ መንገዶች፣ ማራኪ የእግር ጉዞ ትራኮችና ማራኪ የፓርክ አገልግሎቶች ቱሪስቶች በሀገራችን የሚቆዩበትን ጊዜ እንዲያራዝሙና በቆይታቸውም የልብ እርካታን እንዲያገኙ የሚያስችሉ የለውጥ አውታሮች ሆነዋል። ውበትና ጥራት፣ ምቾትና ደህንነት ሲደመሩ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ እያደረጓት ነው። ለዚህም በቅርቡ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ አበባ በመገኘት መደነቃቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የቱሪዝም ልማት ለእኛ ቁሳዊ ገቢ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ያለው የስትራቴጂ ዘርፍ ነው። በአንድ በኩል፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና ለሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድልን በሰፊው በመክፈት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት የዲጂታል አቅምና ቴክኖሎጂ ጋር ተዳምሮ፣ ሀገራችንን የዓለም የሥራ፣ የጉባኤና የዕረፍት መዳረሻ በማድረግ የሀገርን ገጽታ በአዲስ መልክ እየገነባ ይገኛል።
ሲጠቃላል የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትንሳኤ የመንግሥት የፖሊሲ ውጤት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋና የዘርፉ ባለሙያ የጋራ ጥረትና የቅንጅት ፍሬ ነው። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ ነባሩን ጥንታዊ ቅርስ ከአዲሱ የፈጠራ ስራ ጋር ደምረን፣ ኢትዮጵያን የዓለም የቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ የምናደርገው ጉዞ አሁን ካለንበት ከፍታ በላይ እንደሚሻገር ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለንም። እናም እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሩን በመወከል ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ትርክትና የልማት ፍሰት በዓለም አደባባይ ማስተጋባትና ማሳወቅ ይጠበቅበታል።
የሀገራችንን አዲስ ትንሳኤ በጋራ እናብስር።
#የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል