የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ፤ እንደገና አበበ (ዶ/ር)
በሀገራችን ለ38ኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት “ቱሪዝም ለዘላቂ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በሚገኙ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ሲካሄድ የቆየው ተንቀሳቃሽ የቱሪዝም አውደ-ርእይ ማጠቃለያ መርሀግብር በቦሌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተካሄዷል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) እንደገለፁት አውደ-ርእዩ አራት በትምህርት ቤቶች ሲካሄድ ዓለማ ያደረገው ተማሪዎች የሀገራቸውን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲያውቁ፣ እንዲያደንቁ፣ እንዲመራመሩ እና የጉብኝት ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ከትምህር ቤቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በትምህርት ቤቶች ሲያካሄደው የቆየው ተንቀሳቃሽ አውደ-ርዕይ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች ስለሀገራቸው፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ተፈጥሮና ሌሎችም የቱሪዝም ሀብቶች ያላቸውን ግንዛቤ ሊጨምር የሚችል ስራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተማሪዎች እና የመምህራን በበኩላቸው አውደርእዩ ትምህርታዊ ይዘት ያለውና በልጆች አእምሮ ውስጥ ለሀገር ውበት ልዩ ፍቅር የሚፈጥር እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአራት ትምህርት ቤቶች በተካሄደ አውደ-ርእይ ከ7000 በላይ ተማሪዎች በመጎብኘት የሀገራቸውን ማንነት እና ውበት ለማወቅ እድል የፈጠረ እንደሆነ ተገልጸዋል።
ተንቀሳቃሽ አውደ-ርዕዩን የቱሪዝም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።