ብሔራዊ ፓርኮችና በውስጣቸው የሚገኙ የዱር እንስሳት ጥበቃን ይበልጥ በማጠናከር የቱሪዝም ዘርፉን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ ነው
ብሔራዊ ፓርኮችና በውስጣቸው የሚገኙ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ጥበቃን ይበልጥ በማጠናከር የቱሪዝም ዘርፉን የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
 
 
 አለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ተከብሯል።
 
ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን የሚሰጡ ሬንጀሮችን ለማሠብ ዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን በየዓመቱ በሐምሌ ወር እንደሚከበር በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
 
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ ብሔራዊ ፓርኮችና በውስጣቸው የሚገኙ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ጥበቃን ይበልጥ በማጠናከር ለቱሪዝም መስህብና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
በፓርኮች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ጉዳዮችን በመከላከል የጥበቃውንና የልማቱን ሥራ በማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ ምጣታቸውን አመልክተዋል።
 
በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን የዚሁ ጥረት አካልና በዘርፉ የተጎዱ ሬርንጀሮችን ለማስታወስ ያለማ መሆኑን ተናግረዋል።
 
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰው ሰራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው።
 
 
በተለይ ህገ-ወጥ ሰፈራ፣ አደንና ሰደድ እሳት በፓርኮቹ ላይ ጉዳት በማድረስ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ተግዳሮቶችን ለመከላከል ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 34 ሬንጀሮችን በማስመረቅ ዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ቀን መከበሩ የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
 
የሬንጀሮች ቀን ማክበር በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ዘርፍ ለጉዳት የተጋለጡ ሬንጀሮችን ከማስታወስ ባሻገር የሚደረገውን የጥበቃ ሥራ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
 
የዓለም አቀፍ የሬንጀሮች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ክርስቶፈር ጁሊያርስ፣ ኢትዮጵያ ለፓርኮችና የተፈጥሮ ኃብት የምታደርገው እንክብካቤ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
 
ለሶስት ወራት ሰልጥነው የተመርቁት ሬንጀሮች የዚሁ ጥረት ማሳያና የፓርኮችን ጥበቃ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።
 የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ሻሚል ከድር በበኩላቸው፤ በፓርኩ ለሶስት ወራት በጥበቃ ሥነ-ምግባርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰለጠኑ 34 ሬንጀሮች መመረቃቸውን ገልጸዋል።
 
ተመራቂ ሬንጀሮች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ የሬንጀሮች ቀን በመከበሩ መደሰታቸውን ጠቁመው በዘመናዊ መልኩ የተሰጣቸው ሥልጠና ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጥበቃ ሥራን ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
 
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት(ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደጋ አጋዘን ቀይ ቀበሮና ሌሎች በርካታ የዱር እንስሳትና ዕጽዋት መገኛ ነው።
 
በኢትዮጵያ 27 ብሔራዊ ፓርኮች እንደሚገኙ ይታወቃል።