መንግስት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ከባህላዊ ፣ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎች ላይ፣ ዘመናዊ መዋቅሮችን እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ አዲስ የኢኮኖሚ ምሰሶ በማካተት ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል። ይህ የስትራቴጂ ለውጥ፣ ጥንታዊ ታሪካችንን ከዘመናዊነት ጋር በማዋሃድ ሀገሪቱን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ በማድረግ ስኬታማ እንቅስቃሴ ተከናውነዋል።
በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ የተጀመሩት ዘመናዊ የከተማ ልማት ሥራዎች የቱሪዝም ዘርፉን ገጽታ ቀይሮታል። እንደ አዲስ አፍሪካ የኮንቬንሽን ማዕከል እና የአድዋ ድል መታሰቢያን የመሰሉ ታሪካዊ ቦታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወዳደር ጥራት መገንባታቸው፣ የባህል ጥልቀትን ከዘመናዊ ሥነ-ህንፃ ጋር አዋህዶ ለቱሪስቶች አዲስ ልምድን ሰጥቷል። ይህ አቀራረብ ስብሰባዎችን፣ የማበረታቻ ጉዞዎችን፣ ኮንፈረንሶችን እና ኤግዚቢሽኖችን ያካተተ (MICE Tourism) ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ መሰረት ጥሏል።

የከተማ ቱሪዝሙን የንግድ ገጽታ ለማጠናከር ባለፉት ዓመታት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ዘመናዊ የኮንፈረንስ እና የኤግዚቢሽን ማዕከላትን ገንብቷል። እነዚህ ማዕከላት የውጭ ምንዛሬን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እና የከተሞችን ዓለም አቀፍ ዝና ለመገንባት በዋና መሪነት እየሰሩ ይገኛሉ።
ይህ የልማት እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ብቻ ያልተወሰነ ሲሆን፣ እንደ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ባሉ ከተሞችም በተቀናጀ መልኩ እየተስፋፋ ነው። እነዚህ ከተሞች በተፈጥሮ ፀጋቸው ላይ የከተማ ማዕከል ልማቶችን በማከል፣ የቱሪስት መዳረሻነታቸውን በማዘመን ላይ ናቸው። በተለይ በክልል ከተሞች እየተከናወኑ ያሉት የመናፈሻዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች እና የኮሪደር ልማቶች፣ ጎብኚዎች ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በክልል ከተሞችም ዘመናዊ እና ምቹ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏል።
በተለይ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ትስስር፤ ለአብነት የአየር መንገድ መስፋፋት እና ዘመናዊ የመንገድ ግንባታዎች የቱሪስት መዳረሻዎችን እርስ በርስ በማስተሳሰር፣ ጎብኚዎች በከተሞች የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲያራዝሙ እና በዘመናዊ የኮሪደር ልማትና ፓርኮች ታጅበው እንዲንቀሳቀሱ አስችለዋል። መንግስት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዲጂታል መድረኮች በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ልምድ ቀይሯል። እነዚህ ስራዎች በአካባቢው ማህበረሰብ፣ በተለይም በወጣቶች የኑሮ ደረጃ ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ ይገኛል።
እነዚህ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች በቅርብ ጊዜያት በማህበራዊ ሚዲያ ፈጣሪዎች አማካኝነት በስፋት እየተዋወቁ ይገኛሉ። በተለይም የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን እንደ አዳማ እና ባህር ዳር ያሉ ከተሞችን ውበት በፈጠራ ይዘት ለዓለም የሚያስተዋውቁ ወጣት የይዘት ፈጣሪዎች፣ አገሪቱ ያላትን የቱሪዝም አቅም ተደራሽ በማድረግ የላቀ ሚና እየተጫወቱ ነው። ይህም ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ያላቸውን የቆይታ ጊዜ እንዲያራዝሙ እና አዳዲስ ከተሞችን እንዲጎበኙ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል።
የከተማ ቱሪዝም ጉዞ የዘመናዊነት እና የባህል ውህደት ውጤት በመሆኑ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። መንግስት የጀመራቸውን ሰፊ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብይት ስልት በማጀቡ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት እና በቱሪዝም ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በማረጋገጥ ረገድ የላቀ ዕድል ከፍቷል