ሚኒስትሯ ከዋሽንግተን ዲ.ሲ. እና ከተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች የተውጣጡ የኢትዮ-አሜሪካን የንግድ ምክር ቤት አባላት በቢሯቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንዳሉት አሁን ያለው የኢትዮጵያ ገጽታ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ምቹና ሳቢ ነው፡፡
በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ትኩረት ቱሪዝሙ የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ እያሳየ መሆኑን ጠቁመው የንግድ ምክርቤቱ አባላት ሀገራቸውን በአግባቡና ትክክለኛ መልኳን እንዲታወቅ ማድረግ እና ቀርበው መረጃዎችን በማግኘት መስራት ይጠበቅባችሁዋል ብለዋል፡፡
ሰላማዊት ካሳ የኢትዮ-አሜሪካን የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤልያስ ወልዱ የተመራውን የልዑካን ቡድን ባነጋገሩበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ብሔራዊ የቱሪዝም ብራንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ስለሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ አዳዲስ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችና ያሉትን ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ሚኒስትሯ ያብራሩ ሲሆን ዲያስፖራው በዘርፉ ያለውን ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ካፒታል ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮችና አባላት በበኩላቸው በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ የታየው ለውጥና አዳዲስ መዳረሻዎች መበራከታቸው ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ጠቁመው በዘርፉ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍና የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሐብት በስፋት ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።