የቱሪዝም ሚኒስቴር በዘርፍ ጉባኤው የ2018 ዓ.ም. አፈጻጸም ሪፖርትን በመገምገም ለቀጣይ የሪፎርም ሥራዎችና ለአዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ትግበራ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በጉባኤው ማጠቃለያ የሰጡት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አንደተናገሩት የቀጣይ ሥራዎች ለፖሊሲው ትግበራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር፣ ቴክኖሎጂና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በዘርፉ ማስፋፋት እንዲሁም የቱሪስቶችን ደህንነት ለማጠናከር የአደጋ ጊዜ የቱሪዝም መረጃ ሥርዓት ማቋቋም እንደሚገባ በአጽንዎት አሳስበዋል ።
በተጨማሪም “አንድ ወረዳ አንድ መዳረሻ” መርሀግብር አተገባበር ላይ የመረጃ አያያዝና የሪፖርት ሥርዓት ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፣ በመርሀግብሩም የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ የክልል የቱሪዝም ቢሮና ኮሚሽን አደረጃጀቶች እውቅና ተሰጥቷል።
በዚሁ መሰረት
1ኛ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
2ኛ የደቡብ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ቢሮ
2ኛ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
3ኛ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም
4ኛ የሀረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን
5ኛ የድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት
ከቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ በኩል ሽልማታቸውን ተቀብለዋል ።
በሌላ በኩል የዓለም ቱሪዝም ቀን አከባበርን በማስመልከት “ህይወት በአብያተ መንግስታት” መርሃ ግብር በፋሲል ጊቢ ተካሄደ።
በመርሀ ግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ድኤታ እንደገና አበበ (ዶ.ር ) የተጠሪ ተቋማት፣ የፌዴራልና የክልል መንግስት ኃላፊዎች እንዲሁም የክልል ቱሪዝም ቢሮ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በርካታ የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ የሀገሪቱ ወሳኝ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ በተጨማሪም የበዓላት እሴት፣ የታሪካዊና የባህላዊ ቅርሶች ትርጉም ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም የቱሪዝም ሀብቶችን በመጠበቅ እና በማስተዋወቅ ዘርፉን የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ከክልሎች ጋር የመረጃ ማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ800 በላይ አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ቱሪዝም ቀን አከባበርም የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም እና ቅርሶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ ጠቃሚ አጋጣሚ መሆኑ ተጠቁሟል።