ሚኒስትር ሰላማዊ ካሳ

የቱሪዝም ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ አስታወቁ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የዘርፉ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ እንደተናገሩት የቱሪዝም ዘርፍ ለ10 ዓመት የሀገሪቱ የልማት ዕቅድ ስኬት ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ ሚኒስቴሩ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ነድፎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ፀጋዎችን በመጠበቅ፣ በማልማትና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመሩ የገበታ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች በአዳዲስ እይታ በዘርፉ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ ናቸው ብለዋል።
እንደ ሀገር የቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና ነባሮቹን በማጠናከር ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉንና በዚህም ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
በርካታ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ይሰራል ብለዋል።
በፈረንጆች 2025 በቱሪዝም ዘርፍ 15 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አስታውሰው፣ ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን፣ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ድርሻቸው ጉልህ እንደነበር ተናግረዋል።
በቀሪ ወራትም በየደረጃው ያሉ ተቋማትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማጠናከር፣ ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎችን ለመፍጠርና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ቱሪዝም ከብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አምዶች መካከል ለብልጽግና ጉዞ ስኬት አይተኬ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በክልሉም ሰፊ የቱሪዝም አቅም እንዳለ ጠቁመው፤ በተለይ የረጅም ጊዜ የታሪክ፣ የድንቅ ባህል፣ የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም የብዝሃነት ፀጋ ባለቤት መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
ከክልሉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች፣ ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም ሀብቶች ለሀገሪቱ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመስህብ ስፍራዎቹን በማልማት፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማስፋፋትና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማላቅ የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
አርባ ምንጭ ከተማ በቱሪዝም ሀብቷና በሰላም እሴቷ የደመቀች በመሆኗ ለቱሪዝም ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላት የገለጹት ደግሞ የከተማዋ ከንቲ መስፍን መንዛ(ዶ/ር) ናቸው።
በከተማዋ እየተገነባ ያለው የገበታ ለትውልድ ኮንፍረንስ ሪዞርት ለዘርፉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቅሰው፣ የመስህብ ስፍራዎችን በማልማት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር የዘርፉ ተጠሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ዘገባው የኢዜአ