በቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ እና በፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ የተመራው የላሊበላ መካነ ቅርስ ጥገና ክትትል ኮሚቴ ዛሬ ምክክር አድርጓል።
ውይይቱ በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ በሚከናወነው የላሊበላ መካነ-ቅርስ የእድሳት ፕሮጀክት ሂደት ላይ ያተኮረ ሲሆን የጥገና ሥራ ጥናትን በተመለከተ የወጣው ዓለም አቀፍ የጨረታ ሂደትና አጠቃላይ የጥገና ሥራውን በተመለከተ በሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት ዙሪያ ዝርዝር ምክክር ተደርጓል::
 
ሚንስትሯ ሰላማዊት ካሳ የፈረንሳይ መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
የላሊበላ መካነ-ቅርስ እንክብካቤ፣ የታላቁ ቤተመንግስት እድሳት እንዲሁም ብሄራዊ ሙዚየምን ለማዘመን የተጀመረውን ስራ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል::
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፣ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና የላሊበላ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የተካተቱበት አማካሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም ሚንስትሯ ገልፀዋል::
በውይይቱ የስልጠና መድረክ እንዲመቻችም አቅጣጫ ተቀምጧል።
 
የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው የላሊበላ ቅርስ እንክብካቤ የሚመለከቱ ስራዎች በተለይም የታቀደው ጥናት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
 
በውይይቱ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ላሊበላ ደብር የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ የላሊበላ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር ሀላፊዎች ተገኝተዋል::