የቱሪዝም ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር በመተባበር ቡናን በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻነት ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት የሚያስችል ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በጅማ ከተማ አካሂዷል።
ይህ መድረክ በዋናነት የተበታተኑ የቡና ማስተዋወቅ ስራዎችን በቅንጅት ለመምራትና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
የሚኒስቴሩ የመዳረሻና የቱሪዝም ምርት ልማት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሳ ከድር በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብትሆንም ቡናን እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት በመጠቀም ረገድ እስካሁን ከፍተኛ ክፍተት ነበረ። በመሆኑም ይህ አዲስ ፕሮጀክት ቡናን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር የሀገሪቱን የቱሪዝም አማራጮች ለማስፋፋትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የጃይካ ተወካይ ኮጂማ በበኩላቸው ጃፓንና ኢትዮጵያ በቡና ንግድ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ቡናን ከምርትነቱ ባለፈ ለቱሪዝም ግብዓትነት ለመጠቀም ሰፊ ዕድል እንዳለው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው፣ መድረኩ በክልሉ የሚገኙ የቡና ኮሪደሮችን ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች በሚስብ መልኩ ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል። ይህም በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት አክለው ገልጸዋል።
በጉባኤው የቀረበው ጥናት ጎብኝዎች ከቡና እርሻ እስከ ቅምሻ ድረስ ያለውን ሂደት በአካል እንዲመለከቱ የሚያስችል ስልት ያካተተ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በብራንድነት ለማስተዋወቅ ያግዛል ተብሏል።
በሴሚናሩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም የቡና ቱሪዝም ማዕቀፉ ተግባራዊ ሲሆን ለአምራቾች አዲስ የገቢ አማራጭ እንደሚፈጥርና የሀገሪቱን የቡና ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።