ለጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆኑ ብርቅዬ አትሌቶች ያፈራችው ቦቆጂ ከስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን ይሰራል። የቱሪዝም ሚንስቴር

አራተኛ አመቱን ያስቆጠረውና በዘንድሮው የ’ልወቅሽ ኢትዮጵያ’ ተከታታይ ውድድር ሶስተኛ መዳረሻ የሆነችው ቦቆጂ ከተማ ውድድሩን በድምቀት አጠናቀቀች።

በአርሲ አባቶች ባህላዊ ምርቃት የተጀመረው የዛሬው ውድድር ከአትሌቶች ጠንካራ ፉክክር ባሻገር የጤና ሯጮች የ12 ኪ.ሜ. ውድድር ተከናውኖበታል።

በወንዶች ጃፈር ጀማል እንዲሁም በሴቶች ዴንማርካዊቷ ስቲነ ማርች አሸናፊ ሆነዋል።የማጠቃለያ መልዕከት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ እንደገለፁት የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ብሎም ለጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆኑ አትሌቶችን ባፈራችው ቦቆጂ ከተማ ውድድሩን ማዘጋጀት በመቻሉ እንዲሁም የከተማው ህዝብ ላደረገው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ክብርት ሚንስትሯ አክለውም የድንቅ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነቸውን ቦቆጂ ይህ ውድድር ሲያካሂድ ከተማዋን ለዓለም ማስተዋወቅ ፣ ያላትን ቱሩፋቶች አጉልቶ ማሳየት እንዲሁም በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚ ከሚንቀሳቀስበት የስፖርት ቱሪዝም ተጠቃሚ የምትሆንበትን እድል ለመፍጠር እንደሆነ ገልፀዋል።

በዝግጅቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ፣ ሚኒስትር ዲኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ፣ የአርሲ ዞን መስተዳደር አስተዳደር አቶ ኢብራሂም ከድር እንዲሁም የቦቆጂ ከተማ ከንቲባ አቶ በዙ አበበ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ13 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ፤ ወደ 75 የሚጠጉ ተሳታፊዎች ከአዲስ አበባ ወደ ቦቆጂ ተጉዘዋል።የ’ልወቅሽ ኢትዮጵያ’ ተከታታይ ውድድር ቀጣይ እና የዚህ አመት የመጨረሻ መዳረሻ አርባምንጭ ከተማ ስትሆን ውድድሩ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ይደረጋል።