ሀገራችን በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች 18 ደርሰዋል – የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ መመዝገቡን ምክንያት በማድረግ የደስታ ማብሰሪያ መርኃ ግብር በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ተካሂዷል።
 
በመርኃ ግብሩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ “‘ጊፋታ’ ከወላይታ ህዝብ አልፎ߹ ከኢትዮጵያም ተሻግሮ የዓለም ህዝቦች አኩሪ እሴት ሆኖ የተመዘገበ ድንቅ እሴት ነው” ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በብዝኃነት የተሟሸች፣ በህብረ ብሔራዊነት የደመቀች በታሪክ እና በተፈጥሮ የተዋበች ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ታይተው የማይጠገቡ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ሀብቶችን አምቃ የያዘች ሙዚየም ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
የወላይታ ህዝብ የዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል ከእነዚህ ብርቅዬ እሴቶች መካከል አንዱ እንደሆነም ነው የጠቀሱት፡፡
በዓሉ ሰዎች እና እንስሳት በደስታ የሚፈነድቁበት ዕለት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የወላይታ ሕዝብ ጊፋታን እሴቱ ሳይሸራረፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማቆየቱ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
 
ጊፋታ በይፋ በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ ሀገራችን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች 18 መድረሳቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።
 
የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን ቀዳሚ የኢኮኖሚ ዘርፍ በማድረግ በትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ ቀደም እምብዛም የማይታወቁ ስፍራዎችን በማልማት ከዘርፉ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያውያን በታሪክ የተሳሰሩና እንደ “አለላ ቀለም” በልዩነት የደመቁ ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን አጣምራ የያዘች “ክዳን አልባ ሙዝየም” መሆኗን አስረድተዋል። እነዚህ ሃብቶች የጥንት ስልጣኔ አሻራና የወደፊት የብልፅግና ተስፋ መሆናቸውንም አክለዋል።
 
ጊፋታ ከሀገሪቱ ብርቅዬ እሴቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ክብርት ሰላማዊት ካሳ፣ በዓሉ የክረምት መውጣትንና የአዲስ ዘመን መባቻን የሚያበስር ታላቅ ባህላዊ ክንውን መሆኑን ገልጸዋል። በዓሉ የወላይታ ህዝብ አካባቢውን ከቆሻሻ፣ ልቡን ደግሞ ከጥላቻና ከጥል በማንፃት በፍቅር ማዕድ የሚሰባሰብበት ልዩ ዕለት መሆኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም፣ የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ የሀገሪቱን ባህላዊ ፀጋዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርና የሽማግሌዎች ምርቃት የሚፈስበት ይህ እሴት ተጠብቆ ለትውልድ መሻገር እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።