በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቱሪዝም ሚኒስቴርን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እየገመገመ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ጋር በጋራ በማቀድና በመገምግም ወደ ስራ መግባታቸውን በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡


በሩብ ዓመቱ የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት መጠን 250,000 ለማድረስ ታቅዶ 376,615 ቱሪስቶች ሀገራችንን የጎበኙ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ36,370 ጭማሪ ማሳየቱን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ 0.938 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ እና አፈፃፀሙ ከ100 ፐርሰንት በላይ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በመገኘት የሀገራችንን የቱሪዝም ሀብቶች በስፋት የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱም ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአገር ውስጥ ጎብኝዎች መጠን 15 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ 23.5 ሚሊዮን ጎብኝዎች የተንቀሳቀሱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡


ከሀገር ውስጥ ቱሪዝም ገቢ አንጻር 26.06 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዶ 32 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የዱር እንስሳት ዘርፍ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የጤና አገልግሎትን ከማስፋፋት አንጻር አራት ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በትብብር ለማካሄድ ታቅዶ ሁለቱ መከናወኑ ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን እና በክልሎች ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች 200 ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ለመመዝገብ ታቅዶ 407 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በሌላ በኩል 50 ቋሚ ቅርሶችን ለመመዝገብ ታቅዶ 76 ቋሚ ቅርሶች መመዝገባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡