የሉሲና ሰላም ቅሪተ አካሎች ለታሪክ አጥኚዎች የሚሰጠው ዕድል ትልቅ ነው አሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፡፡
የሉሲ እና ሰላም ኤግዚቢሽን በዛሬው ዕለት በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ከተማ ክፍት ሆኗል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሉሲና ሰላም ቅሪተ አካሎች በቼክ መገኘት ለታሪክ አጥኚዎች የሚሰጠው ዕድል በዋጋ የማይተመን ነው፡፡

የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፒተር ፊያላ በበኩላቸው፤ የሰው ልጅ አመጣጥን ለሚያሳየው ኤግዚቢሽን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ሙዚየም እየተካሄደ የሚገኘው ኤግዚቢሽን ለሁለት ወራት የሚቆይ ሲሆን ሚኒስትሯ ኢትዮጵያን መጥታችሁ ጎብኙ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የህፃናት ሙዚየም ለማቋቋም ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ስምምነት አድርገዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ከቼክ ብሔራዊ ሙዚየም እና ከቼክ ዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋር ስምምነቱን በፕራግ ከተማ ተፈራርመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት ቁጥር 2 ፓርክ ውስጥ ለሚገነባው የህፃናት ሙዚየም የቼክ ሪፐብሊክ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሯ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
የህፃናት ሙዚየሙ ህፃናት ቀለል ባለ መንገድ ስለ ሀገራችን ታሪክ እና ባህል እውቀት እንዲኖራቸው ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የቼክ ሪፐብሊክ መንግስት ይህንን ሙዚየም ለማቋቋም ለሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።