መስቀልና ቱሪዝም

ሌሎች ሀገራት የመስቀልን በዓልን ቢያከብሩም በኢትዮጵያ የሚከበረው የመስቀል በዓል የሚከበረው  ከሌሎች ሀገራት በደመቀና በላቀ ሥነ ሥርዐት ነው፡፡  ብሔረሰቦች መስቀልን እንደየባህላቸው፣ ወግ እና አኗኗር ያከብራሉ፡፡ የመስቀል በዓል ከመንፈሳዊ ተልዕኮው በላይ በረጅም ዘመናት የኢትዮጵያዊነት አብሮነት ውስጥ ባህላዊ እሴት ሆኗል፡፡ መስቀል በየብሔረሰቡ የተለያየ ስያሜ አለው፡፡ በጉራጌ ‘’መስቀር’’፣በሃድያ፣ በዳውሮ፣ ወላይታና ጋሞ ብሄረሰቦች ደግሞ ‘’መስቀላ’’ ተብሎ ይጠራል፡፡ በከምባታ ‘’መሳላ’’፣ በየም ‘’ሄቦ’’፣በኦሮሞ ደግሞ ‘’ጉባ’ ተብሎ ይጠራል፡፡ በሻኪቾ እና ካፊቾ ብሔረሰቦች ደግሞ ‘’መሽቀሮ’’ የሚል ስያሜ አለው፡፡ አማራና ትግሬዎች ደግሞ ‘’መስቀል’’ ብለው እንደሚጠሩት የኢንታንጀበል ባህላዊ ቅርስ (ኢባ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመመዝገብ የተዘጋጀው ኢንቬንተሪ ፎርማት ያመለክታል፡፡ ፡፡       

የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNISCO) እውቅና ተሰጥቶት በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ ኮቪድ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከመዛመቱ በፊት በርካታ ቱሪስቶች የመስቀል በዓልን ለመታደም ይመጣሉ፡፡ ቁጥራቸው ቢቀንስም አሁንም ይመጣሉ፡፡

የመስቀል ደመራ የሚደመረው መስከረም 16 ቀን ነው፡፡ ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል በማለት ዓምደ ተዋሕዶ የሚባለው ገጸ ድር አመልክቷል፡፡  

‘’መስቀልና ደመራ – ደመራና መስቀል’’ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የደመራ ስርዐት ተመሳሳይ ቢሆንም መስከረም 16 ቀን ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረው የደመራ ስርዓት ደማቅ እና ማራኪ ነው፡፡

መስቀል የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን ከመግባቱ በፊት ይከበር የነበረው በመቶ ሺ ዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ እና አካባቢው ኗሪዎች በሚገኙበት ስርዓት ነበር፡፡ በበዓሉ ላይ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶችና ቱሪስቶችም ይገኛሉ፡፡ ጥንግ ድርብ የለበሱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሽብሸባና ያሬዳዊ ዜማ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ዝማሬና ሽብሸባ፣ በዓሉን አስመልክቶ በሠረገላ የሚጎተት (የንግሥት እሌኒ) ተምሳሌት፣የፌዴራል ፖሊስ ሙዚቃ ባንድ ማርሽ እና ሌሎች ዝግጅቶች ለበዓሉ ድምቀት ሰጪ ናቸው፡፡ ልብሰ ተክህኖው፣ ዝማሬው፣ወይዛዝርትና ጉብሎች የሚለብሱት ጸሐዳ ልብስ ልብ ሰራቂ ከሆነው ውበትና ደም ግባታቸው ጋር ተዳምሮ ቀልብ የሚስቡ ትዕይንቶች ናቸው፡፡ የጎበዛዝት ‘’ኢዮሐ አበባዬ፣ መስከረም ጠባዬ’’ መዝሙር እና የሴቶች ‘’እልልታ’’ አየሩን በደስታ ይሞላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዓሉን አስመልከተው ሃይማኖታዊ ትምህርት፣ አባታዊ ምዕዳን እና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ደመራውን ባርከው በስነ ስርዓቱ ላይ ከሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ አመራር ጋር በመሆን በችቦ ደመራውን ይለኩሳሉ፡፡ በሩቅ የሚጋረፈው የደመራው ነበልባል እሳት ወላፈን በሰማዩ ላይ የሚበተነው የእሳት ፍንጥሪ በደስታ ያጥናል፡፡

መስከረም በአበባው ሠርግ በጭብጨባው” ይታወቃል

መስከረም አበቦች በየመስኩ የሚፈነዱበት፤ አደይ አበባ ምድሪቱን የሚያለብስበት ወር ነው፡፡ መስከረም አንድ የዘመን መለወጫ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በመሆኑ ወርኃ አደይ፣ ወርኃ ጽጌ ይባላል፡፡ የአዲስ ዓመት ተስፋ ወር ሲሆን ዕንቁጣጣሽ፣የመስቀል በዓል እና እሬቻ የመሳሰሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል፡፡

መስቀልን በደቡብ ኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ክዋኔው ይልቅ ባህላዊ ገፅታው ጎልቶ በታላቅ ዝግጅትና ድምቀት ይከበራል፡፡ እሬቻም በመስከረም ወር በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በታላቅ ዝግጅትና ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡

ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር እንደሚለው በአገራችን የመስቀል በዓል መለያና ዓርማ የኾነው ደመራው ነው፡፡ በመስቀል በዓል እረኞችና ወጣቶች የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይጫወታሉ፤ እናቶችና አባቶችም በተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይኾናሉ፡፡ ሕዝቡም በየጎጡና በየሰፈሩ በነቂስ በመውጣት የደመራ በዓሉን በድምቀት ካከበረ በኋላ በኅብረት እየተመገበና እየጠጣ ስላለፈው ክረምትና ስለመጪው መኸር ጉዳይ የሚጨዋወትበት ልዩ አጋጣሚ ሲሆን የሀገር ሽማግሌዎች ሰብሰብ ብለው የሚወያዩበት ዕለት ነው፡፡

የመስቀል በዓል ሰዎች በክረምት ምክንያት እርስ በርስ ተለያይተው ከከረሙ በኋላ የሚገናኙበት፣ እሸት የሚደርስበትና የሚቀመስበት፣ የዘርና የአረም ሥራ የሚያበቃበት፣ገበሬው ከአድካሚው የክረምት ሥራ ተላቆ አንጻራዊ ዕረፍት የሚያገኝበት በመኾኑ ተለያይቶ የከረመው ወዳጅ ዘመድ ለመጨዋወትና ለመገናኘት ያመቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የመስቀልን በዓል የሚያከብሩት ብቻቸውን አይደለም፤ ዕፀዋቱም፣ እንስሳቱም ምድሪቱም ሰማዩም ከሰው ጋራ ተስማምተው ተዋሕደው ያከብሩታል በማለት ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር ገልጿል፡፡

መስቀል በደቡብ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዝግጅትና ድምቀት የሚከበር ሲሆን የበዓላት ሁሉ አውራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለአብነት ጉራጌዎች መስቀልን እንዴት እንደሚያከብሩ እኤአ መስከረም፡
26/2018 ‘’መስቀል በቤተ-ጉራጌ’’ በሚል ርዕስ ቢቢሲ የአማርኛው ገጸ ድር ያወጣው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው መስቀል በቤተ- ጉራጌ የአንድ ቀን በዓል አይደለም፡፡ ከ10 ቀናት በላይ ይወስዳል፡፡ከመስከረም 12 በፊት የጉራጌ ብሄር ተወላጆች፤ ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ትውልድ ስፍራቸው ይተማሉ፡፡ምክንያቱም መስቀል በጉራጌ ሃይማኖታዊ በዓል፣ የመተጫጫ ወቅት፣ የእርቅ እና የአንድነት አውድ ስለሆነ ‹‹መች በደረሰ የሚያስብል ወቅት›› ነው፡፡

መስከረም 13 ‘’ወሬት ያህና’’ በተሰኘው የበዓል መክፈቻ መሰናዶ ሰሞነ መስቀል ይጀመራል፡፡ ወሬት ያህና ጉጉት እና ናፍቆት የፈጠረውን እንቅልፍ አልባ ቀን የሚዘክር ቃል ነው፡፡ መስከረም 14 የእርድ ዋዜማ ሲሆን የልጆች የደመራ ፣ የሴቶች የአይቤ እና ጎመን ቀን ይባላል፡፡ ቤቶች የሚሰነዳዱበት የእንፋሎት ቆጮ የሚቀርብበት ቀንም ነው፡፡ መስከረም 15 ዋናው የጉራጌ የመስቀል በዓል ‘’ወኀምያ’’ ነው፡፡ በዚህ ዕለት እርድ ይፈጸማል፡፡መስከረም 16 ‘’ምግይር’’ ወይም ደመራ የሚባለው ቀን ነው (የአባቶች ደመራም ይባላል)፡፡ በየቤቱ፤ ጠዋት የህጻናት ማታ ደግሞ የአባቶች ደመራ ይለኮሳል፡፡ በዚህ ዕለት ከብቶች ከቤት አይወጡም፡፡

የመስቀል በዓል በጎ ገጽታ

መስቀል በዓል በክረምት ምክንያት እርስ በርስ ተለያይተው የከረሙ ሰዎች የሚገናኙበት፣ እሸት የሚደርስበትና የሚቀመስበት፣ የዘርና የአረም ሥራ የሚያበቃበት፣ገበሬው ከክረምቱ አድካሚ ሥራ ተላቆ አንጻራዊ ዕረፍት የሚያገኝበት በመኾኑ ተለያይቶ የከረመው ወዳጅ ዘመድ ለመጨዋወትና ለመገናኘት ያመቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የመስቀልን በዓል የሚያከብሩት ብቻቸውን አይደለም፤ ዕፀዋቱም፣ እንስሳቱም ምድሪቱም ሰማዩም ከሰው ጋራ ተስማምተው ተዋሕደው ያከብሩታል በማለት ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር ገልጿል፡፡

የመስቀል በዓል በርካታ ቱሪስቶች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ስለሆነ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

መስቀል ተለያይተው የነበሩ የቤተሰብ አባላት፣ወዳጆች እና ዘመዳሞች ተገናኝተው ችግሮቻቸውን የሚያቃልሉበት፣የተጣሉና፡የተቀያየሙ፡የሚታረቁበት፣በአዲስ ዓመት አዲስ የግልና የቤተሰብ ዕቅድ የሚታቀድበት፣ወጣቶች የአባቶችን፣የሽማግሌዎችን እና የባልቴቶችን ምርቃት የሚቀበሉበት፣ኪነ ጥበብ (ዘፈን፣ ሙዚቃ፣ስነ ቃል..)ጎልቶ የሚወጣበትና፡ የሚታይበት ስለሀገር የሚጸለይበት እና እርስ በርስ መተሳሰብና ፍቅር የሚነግሥበት በዓል ነው፡፡   በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት እውቅና ተሰጥቶት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የመስቀል በዓል፣በዂነት ቱሪዝም (MICE Tourism) ትኩረት ተሰጥቶት ቱሪስቶችን በመሳብ የሀገራችንን ኢኮኖሚና ገጽታ ለመገንባት ልናውለው ይገባል፡፡

Leave a Comment